ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀቁ
ሰኞ፣ ሐምሌ 9 2010ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመደን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ለኤርትራዉ የልዑካን ቡድን አሸኛነት አድርገዉላቸዋል።
በሌላ በኩል ለሃያ ዓመታት ግድም ተዘግቶ የነበረዉ አዲስ አበባ ላይ የሚገኘዉ የኤርትራ ኤምባሲ ዳግም ተከፍቶአል። ኤምባሲዉን በይፋ የከፈቱት የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እና የኤርትራዉ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ናቸዉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የኤርትራን ልዑካን ቡድንን ቦሌ ዓለም አአፍ አዉሮፕላን ጣብያ ተገኝኝተዉ ከሸኙ በኃላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ « ልዑካን ቡድኑ በተለይ በአዲስ አበባና ሀዋሳ ጥሩ የሚባል ጊዜን ማሳለፋቸዉን ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ከተማና አካባቢዋ የሚኖር ሕዝብ ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ ከአዉሮፕላን ጣብያ ጀምሮ እስከ ቤተ መንግሥት በከፍተኛ ደስታና ፍቅር፤ በፈረስ የታጀበ ደማቅ አቀባበል፤ የአዲስ አበባን እና አካባቢዋን ሕዝብ ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ሲሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መልክታቸዉን አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤርትራ ከፍተኛ ልዑካን ቡድንና የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በሀዋሳ ለነበረዉ ቆይታ ፤ የሀዋሳ ከተማ ሕዝብ እጅግ የሚያምረዉን ባህሉን ተጠቅሞ፤ ማራኪና አስደሳች አቀባበል ስላደረገ አመስግነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀዋሳ ከተማ ነዋሪ በተጨማሪ በሀዋሳ ከተማ መግብያ ላይ ሆኖ አቀባበልና አሸኛነት ያደረገዉ የጥቁር ዉኃ ሕዝብ የሻሸመኔ ሕዝብ በየመንገዱ ዳር ቆሞ ላሳየዉ ፍቅርና ላሳየዉ አክብሮት እና እንግዳ ተቀባይነት ከፍ ያለ ምስጋናቸዉን አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ የተደረገዉ ሞቅ ያለ ዝግጅት « እንደተባለዉም የጥላቻን የቂምን የክፉ ሃሳብን ግንብ ያፈረስንበት በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ሊገነባ የሚገባዉን ድልድይ ዳግም ሊናድ እንዳይችል ጠንካራ ሆኖ እንዲገነባ ያደረግንበት፤ አስደናቂ ምሽት ነበር ፤ ለዚህም ተሳታፊ ወገኖችን ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ ሲሉ ተናግረዋል። « በተለይ ፕሮግራሙን ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ስትሉ የነበራችሁ የፀጥታ አካላት የዉጭ ጉዳይ ሠራተኞች ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ሠራተኞች፤ እንዲሁም ሌላ ተባባሪ አካላት በሙሉ እንዲሁም ታዋቂ አርቲስቶች ላደረጋችሁት እጅግ የሚደንቅ ሃገራዊ ፍቅር እና ክብር ላቅ ያለ ምስጋና ላቀርብ እፈልጋለሁ። በተለይ አርቲስት አሊ ቢራና ፤ ጋሽ ማሕሙድ አሕመድ እያመማቸዉ ለሕዝባቸዉ ያላቸዉን ክብር ለማሳየት ያደረጉትን አስደናቂ ሃገር ወዳድ ጋ መሆናቸዉን የማይናወጥ ለምንግዜም የሚዘልቅ ብቃት መሆኑን ስላሳዩ በሕዝብ ስም ላመሰግናቸዉ እወዳለሁ» ብለዋል።
አዜብ ታደሰ