በሳውዲ አረቢያ እሥር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ጥሪ
ረቡዕ፣ ጥር 22 2016በሳውዲ አረቢያ እሥር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ጥሪ
ሳውዲ አረቢያ ውስጥ በተለያየ ወንጀል ተጠርጥረውና ተፈርዶባቸው በእሥር ቆይተው የፍርድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ ባለመመለሳቸው ለሌላ እሥር ተዳርገው በችግር ላይ እንደሚገኙ ገለፁ።
በሳውዲ አረቢያ እስከ ዘጠኝ ዓመት ድረስ ታስረው ቆይተው ፍርዳቸውን የጨረሱ ከመካከላቸው እንደሚገኙ የገለፁት እኒሁ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ታሳሪዎች መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ሊመልሳቸው አለመቻሉን ጠቅሰው በዚህ ምክንያት ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
በሳውዲ አረቢያ በችግር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለማስመለስ የተያዘው የአንድ ዓመት የመንግሥት እቅድ 131 ሺህ ዜጎችን በማስመለስ መጠናቀቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ በፊት ገልጾ ነበር።
የእሥረኞቹ የድረሱልን ጥሪ
በስደት ለተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደው እንዲሁም ሳያውቁ በደላሎች ውትወታ እና ማማለያ ተገፍተውወደ መካከለኛው ምስራቅ በተለይም ወደ ሳውዲ አረቢያ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያንለተደራራቢ እንግልት እና ችግር ይጋለጣሉ። መንግሥት ከሳውዲ አረቢያ ከ 100 ሺህ በላይ የእሥር ፍርዳቸውን የጨረሱትን ዜጎች ባለፈው አመት ወደ ሀገር ቤት ቢያጓጉዝም አሁንም ከእሥር ወጥተው ለሌላ እሥር የተዳረጉ እስከ ስድሳ ሺህ የሚሆኑ ዜጎች በአስቸጋሪ እሥር ቤት ውስጥ በችግር ላይ መሆናቸውን ስማቸውን ለደህንነታቸው ሲሉ መግለጽ ያልፈለጉ ታሳሪዎች ያገኙትን ድንገተኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቅመው ችግራቸውን ገልፀዋል። ኢትዮጵያውያኑ መንግስት ወደሃገራቸው እንዲመልሳቸውም ተማጽነዋል።
መንግሥት በሳውዲ አረቢያ በችግር ውስጥ ይኖሩ ከነበሩ ዜጎች መካከል 131 ሺህ ያህሉን ማስመለሱ ይታወሳል።
በወቅቱ ሲመለሱ ካነጋገርናቸው መካከል ኡመር የተባለው ወጣት ሰባት ዓመታትን ሳውዲ አረቢያ ኖሮ በስተመጨረሻ በሕግ አስከባሪዎች ቁጥጥር ሥር ውሎ 10 ወራትን በእሥር አሳልፋል። ወጣቱ ሀገሩ ቢገባም መንግሥት ለቀሩት እንዲደርስላቸው ጠይቆ ነበር። "እዛ ያሉ ወንድሞቻችን አሁንም በስቃይ ላይ ነው ያሉት። ዳግመኞ በረራ እንዳይቋረጥ በሚል በጭንቀት ላይ ነው ያሉት" ነበር ያለው።
በወንጀል ተጠርጥረውና ተከሰው ዋናውን የፍርድ ጊዜያቸውን ጨርሰው ሳለ መንግሥት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ባለማድረጉ ለሌላ እሥር ተዳርገው የሚገኙት እነዚህ ሰዎች አሁን ታሥረው የሚገኙበት ሥፍራ ለከፋ ጭንቀት እንደዳረጋቸው ተናግረዋል።
መንግሥት የማስመለስ ሥራውን ዳግም እንዲጀምር መጠየቁ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ እአምባሳደር ብርቱካን አያኖ መንግሥት የዲፕሎማሲ መስመሩን በመጠቀም በሳውዲ አረቢያ በችግር ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ አያያዛቸው እንዲሻሻል መንግሥት ዝም አለማለቱን ከዚህ በፊት ተናግረው ነበር። ይሁንና አሁንም 69,000 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በማቆያ ቦታዎች ሆነው የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
አዜብ ታደሰ