የ50 አኅጉራዊ የሲቪክ ድርጅቶች የኢትዮጵያ የሲቪክ ምኅዳሩ እጅግ አሳስቦናል አሉ
ማክሰኞ፣ ጥር 6 201750 በአፍሪቃ እና አውሮጳ የሚንቀሳቀሱ አኅጉራዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት ጠንካራ ሲሺክ ድርጅቶች ላይ የሚወስደውን ያልተገባ ያሉትን ርምጃ እንዲያቆም ጠየቁ ። እነዚህ ከ12 በላይ አገራት የሚንቀሳቀሱ የመብት ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ የተወሰኑ የመብት ድርጅቶች ላይ የጣለውን እግድ በአስቸኳይ እንዲያነሳም ጠይቀዋል ። ድርጅቶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላት የኢትዮጵያ መንግሥት በሲቪክ እና የመገናኛ ብዙኃን ዘርፎች ላይ እያደረገ ያለውን ተጽእኖ እንዲያቆም ግፊት እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል ።
የድርጅቶቹ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?
እነዚህ 50 አኅጉራዊ እና መቀመጫቸውን ጄኔቫ ጭምር ያደረጉ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን የመደራጀት መብት ለማስከበር ቁርጠኝነቱን እንዲያረጋግጥ እና ይህም ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን ጭምር ጠቅሰው ጠይቀዋል ። ድርጅቶቹ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ውጥረትና ሥር የሰደዱ ያሏቸውን ግጭቶችን በተመለከተ አለን ያሉትን ጥልቅ ሥጋትም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን "ሥርዓታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማጋለጥ ቁርጠኛ የሆኑትን ሕጋዊ የሲቪል ማህበራትን ለማጥላላት እና ለማዳከም ሆን ብሎ የሚወስደውን" ያሉትንም እርምጃ አጥብቀን እናወግዛለን ሲሉ በፊርማቸው አረጋግጠዋል ። በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ የሚፈጽሙ ወከባዎች እጅግ አሳስቦናል ያሉት እነዚህ ድርጅቶች ይህ አዝማሚያ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲሉ አውግዘዋል። የመብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ያለ ፍርሃት እና ያለ ገደብ ሥራዎቻቸውን እንዲሰሩም ጥሪ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ከሚችሉ አካላት ምን ይጠበቃል?
እነዚህ ድርጅቶች መግለጫ እንዲያወጡ ምክንያት የሆነው በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ የሚባሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መታገድ ነው። ከታገዱት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ድርጅቶቹ "አብዛኞቹ አጋሮቻችን ናቸው" ብለዋል። አክለውም "ያለንበትን ነገር በቅጡ ስለተረዱ በራሳቸው ምልከታ፣ ባላቸው መረጃ ልክ ተመስርተው ነው ይህንን የአጋርነት፣ የድጋፍ እና የአብሮነት መግለጫ እና ሥጋታቸውን ከምክረ ሀሳባቸው ጋር አካተው ለመንግሥት የገለፁት ብለዋል።
እነዚህ ሃምሳ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች የሲቪል ማኅበራት ግልጽ ባልሆኑ እና ከሕግ ውጭ በሆኑ ክሶች እየደረሰባቸው ያለው ችግር በዘርፉ ከዚህ በፊት ተገኝተው የነበሩ ያሏቸውን ውጤቶች የመቀልበስ ሥጋት የደቀኑ ናቸው ። ይህም በመሆኑ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉ አካላት ጠንካራ ግፊት እንዲያደርጉ ሲሉ ጥሪ አድርገዋል ። ለመሆኑ የእነዚህ ተቋማት መግለጫ ምን ያህል ጉልበት ያለው ነው የሚለውን አቶ ያሬድን ጠይቀናቸው ምላሽ ሰጥተዋል።
የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች
የኢትዮጵያ መንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነቱ መብቶችን ማክበርና ማስጠበቅ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል ያሉት ድርጅቶቹ ሆኖም የአፍሪካ የሰብአዊ እና ሕዝቦች መብት ኮሚሽን በተለይም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና የሲቪል ማኅበራትን ጥበቃን በሚመለከት የሚሰጣቸውን ምክሮች መንግሥት ያለማቋረጥ ችላ ብሏል ሲሉ ወቅሰዋል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ድርጅቶች እና መገናኛ ብዙኃን "ከእንቅፋት፣ ከጣልቃ ገብነት እና ከበቀል ነፃ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ክፍት የሆነ ምኅዳር ከሌለ ዘላቂ ዲሞክራሲ፣ ሰላም እና መረጋጋት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደማይኖር እናምናለን" ሲሉም በመግለጫው ሥጋታቸውን አሰምተዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እገዳ በጣለባቸው ሀገር በቀል ሲቪል ድርጅቶች ላይ አሁንም ምርመራ እያካሄደ ነው ያሉት አቶ ያሬድ የሚሰጠንን ምላሽ ውጤት እየጠበቅን ነው ብለዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ