የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ስርዓት ማስከበር አልቻለም አሉ
ሐሙስ፣ ሰኔ 20 2016በትግራይ እየተንሰራፉ ናቸው የተባሉ ሕገወጥ ተግባራት ለማስቆም ግዚያዊ አስተዳደሩ እየሰራ አይደለም ሲሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ። በሴቶች ላይ የሚደረስ ጥቃት፣ ሕገወጥ የመዓድናት ምዝበራ እና የመሬት ወረራ፣ እንዲሁም የተለያዩ ወንጀሎች በክልሉ መንሰራፋታቸው ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል።ለትግራይ ችግር ተቃዋሚዎች ህወሃትን ከሰሱ
በትግራይ የፀጥታ ችግሮች፣ ሕገወጥ ተግባራት እና የተቀናጀ የተፈጥሮ ሐብት ምዝበራ መንሰራፉቱ የሚገልፁት በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች ይህ ለማስቆም የሚሰራ መንግስት አልያም የአስተዳደር አካል አለመኖሩ ደግሞ ችግሩ የተወሳሰበ እንዳደረገው ያነሳሉ። የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ በትግራይ ክልል በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በሕገወጥ መንገድ ወርቅ ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናት እየተመዘበረ ነው የሚሉ ሲሆን፥ በእነዚህ የወርቅ ሐብት ያላቸው አካባቢዎች አገልግሎት ላይ እየዋሉ ያሉ ኬሚካሎችም በዘላቂነት ስነምህዳሩ ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑ በመግለፅ 'ሕገወጥ' ያሉት ተግባር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ አንስተዋል።የሽግግር ሂደት በትግራይ፤ ተስፋና ስጋቶቹ
አቶ ዓምዶም "በጣም አሳሳቢ የሚያደርገው አደገኛ የሚባሉ እና አካባቢው የሚበክሉ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ናቸው። በትግራይ ጦርነት ተሳታፊ የነበሩ እና በርካታ ወንጀል የፈፀሙ የውጭ ሐይሎች ጭምር በትግራይ ወርቅ እና ሳፋየር ምዝበራ እየተሳተፉ መሆኑ ደግሞ ሌላ አደገኛ ነገር ነው። ይህ ችግርና ምዝበራ አሁን ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ጠባሳ ይዞ የሚመጣ ነው። በአሁኑ ሰዓት ይህ ወንጀል ማስቆም የሚችል ዓቅም ያለው መንግስትም የለም" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በሴቶች ላይ የሚደርስ እገታ እና ግድያ፣ በከተሞች የሚፈፀም የተለያዩ ወንጀሎች እንዲሁም በኢንቨስትመንት ስም የተንሰራፋ የመሬት ወረራ በትግራይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸው በተቃዋሚ ፖርቲዎች በኩል ተገልጿል። የስራ ዕድል ያጣ፣ በሀገሩ ተስፋ የቆረጠ ወጣት በትግራይ መበራከቱ፥ ብቸኛ አማራጩ ደግሞ ስደት እየሆነ ነው ያሉት የተቃዋሚው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አሉላ ሃይሉ፥ ችግሩ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት አለመኖሩ ያወሳሉ።
አቶ አሉላ "ጎረቤታችን ኤርትራ ሁናው እንዳለ ለመገዛት የሚመች ህዝብ ብቻ እንዲቀር ስለሚፈለግ፥ ወጣቱ መሰደዱ አሳሳቢ ሆኖ አይታያቸውም ማንም እየሰራም አይደለም። እንደውም ችግሮቹ ባለቤት ስላላቸው፣ ችግሩ እንዲባባስ በማድረግ ወጣቱ ነቅሎ እንዲወጣ የሚያደርግ ስርዓት ነው ያለን" ብለዋል።ትግራይ ክልል ተጨማሪ የተቃዋሚዎች እስር
በትግራይ የተንሰራፉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት መሰረታዊ የስርዓት ለውጥ እንደሚያስፈልግም በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲዎች ገልፀዋል። የባይቶና ከፍተኛ አመራር አቶ ዮሴፍ በርሃ "የስርዓት ለውጣ ሳይመጣ የሚፈጠር ነገር ስለሌላ፣ የሚቆም የሴቶች ግድያ ስለሌለ፣ የሚቀረፍ የፀጥታ ችግር ስለሌለ በመሰረታዊ ለውጥ እንቅስቃሴ ወጣቱ ተሳታፊ እንዲሆን፣ ሚናው ይወጣ ነው የምንለው" ሲሉ ገልፀዋል።
በተለይም ከፀጥታ ችግሮች ጋር በተገናኘ የሚነሱ ወቀሳዎች አስመልክተን ከክልሉ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣና ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የማዓድን ምዝበራ ጨምሮ በክልሉ የተወሳሰቡ በርካታ ችግሮች እና ወንጀሎች እየታዩ መሆኑ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የሚቀበል ሲሆን እነዚህ ለመፍታት እየሰራ መሆኑንም የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በየግዜው ይገልፃሉ።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ሚሊዮን ሃይለስላሴ
ነጋሽ መሀመድ
ፀሀይ ጫኔ