1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ክልል የደራ ወረዳ ጥቃት

ሰኞ፣ መጋቢት 2 2016

አስተያየት ሰጪው በእለቱ በሶስቱ ቀበሌያት ከቆሰሉት በተጨማሪ ብያንስ የ11 ሰዎች ህይወት ህልፈት መሰማቱን አስረድተዋልም፡፡ ከነዚህም ስድስቱን በስም እንደሚያውቃቸው በማስገንዘብ፡ ከቆሰሉት ደግሞ የ11 ዓመት ታዳጊ ሴት እና አበራ መኮንን የሚባሉ የ60 ዓመት አዛውንት ተመልክቻለሁ” ብለዋል አስተያየት ሰጪው፡፡

https://p.dw.com/p/4dOwa
ፎቶ ማህደር፤ ኦሮምያ ክልል ኢትዮጵያ
ፎቶ ማህደር፤ ኦሮምያ ክልል ኢትዮጵያ ምስል Seyoum Getu/DW

በጥቃቱ ሰዎች ተገድሏል

የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የሚዋሰኑበት የሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ታጣቂዎች ፈጸሙት በተባለ ጥቃት የሰው ሕይወት መቀጠፉንና ንብረት መውደሙን የካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪዎች ጥቃቱን በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች አድርሰውታል ብለዋል፡፡
ሥዩም ጌቱባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተከሰተው ምንድነው?
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ነዋሪነታቸውን ያደረጉና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው ግን እንዳይጠቀስ የጠየቁን አስተያየት ሰጪ እንደሚሉት ባለፈው ሳምንት ተደጋጋሚ የታጣቂዎች ጥቃት በአከባቢው ደርሷል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው በተለይም ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. አመሻሽ ከ11 ሰኣት ጀምሮ በወረዳው ሶስት ቀበሌዎች ታጣቂዎች የከፋ ያሉት ውድመት አድርሰዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው የአከባቢ ነዋሪ ፣በነዚህ ቀበሌያት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡ በጥቃት አድራሾቹ ታጣቂዎች የቤት እንስሳትን ጨምሮ ንበረት ተዘርፈው ተወስደዋል፡፡ 
 “በአከባቢያችን የጸጥታ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስከፊ እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለይም የባለፈው ሳምንት የሓሙስ ምሽቱ ጥቃት ሆኖ የማያውቅ ክስተት ነው ያስከተለው፡፡ ከአማራ ክልል ተነስተው ወሰን ተሻግረው የመጡ ታጣቂዎች ናቸው ጥቃቱን የፈጸሙት፡፡ ጅሩ-ዳዳ፣ ወሬ-ገብሮ እና መንቃታ ዋሪዮ በተባሉ ቀበሌያት የከፋ የነዋሪው ህዝብ ቤት ቃጠሎ እና ንብረት ውድመት ፈጽመዋል፡፡ በተለይም ጅሩ ዳዳ በተባለ ቀበሌ ከ90 በመቶ በላይ ቤት ተቃጥለዋል ማለት ይቻላል፡፡ ከ280 ቤቶች በላይ በሶስቱ ቀበሌያት ተቃጥለዋል፡፡ ፍየሎችን ጨምሮ ከ400 በላይ የቀንድ ከብቶች ተዘርፈው ተወስደዋል” ነው ያሉት፡፡


በጥቃቱ ያለፈው የሰው ህይወት


አስተያየት ሰጪው በእለቱ በሶስቱ ቀበሌያት ከቆሰሉት በተጨማሪ ብያንስ የ11 ሰዎች ህይወት ህልፈት መሰማቱን አስረድተዋልም፡፡ ከነዚህም ስድስቱን በስም እንደሚያውቃቸው በማስገንዘብ፡ “ቦጋሌ ጅማ እና አሸብር ጅማ የሚባሉ ወንድማማቾች ወሬ ገብሮ በሚባል ቀበሌ ከአንድ ቤት ነው የተገደሉት፡፡ ደሳለኝ ለማ፣ ሽመልስ ሙዘይን፣ ጌታሁን ጋሪ እና ሃብታሙ ቱሉ የሚባሉ ህይወታቸው ካለፉ ናቸው፡፡ ከቆሰሉት ደግሞ የ11 ዓመት ታዳጊ ሴት እና አበራ መኮንን የሚባሉ የ60  ዓመት አዛውንት ተመልክቻለሁ” ብለዋል አስተያየት ሰጪው፡፡
በአከባቢው የደህንነት ስጋቱ ስፋት
ለደህንነታቸው ስጋት አለኝ ያሉት ስማቸው እንዳይጠቀስና ድምጻቸውንም እንዳንጠቀም ጠይቀው አስተያየታቸው የሰጡን ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ነዋሪም አሁን አሁን በሁለቱ ክልሎች አዋሳን አከባቢ ባለችው በዚህ ወረዳ አስጊ ያሉት የጸጥታ ችግር መኖሩንም አስረድተዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ እስካሁን የተዘረፉትን ንብረት ለማስመለስ እና በአከባቢው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተስተዋለው የጸጥታ ሃይሎች አጸፋም አልታየም፡፡ 
ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ሶስቱ ቀበሌያት ከደራ ወረዳ ዋና ከተማ ጉንዶ መስቀል ወደ ፊቹ በሚወስደው የጀማ ወንዝ አቅራቢያ የሚገኝ እና ከዚህ በፊት መንግስት ሸነ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው የታጠቀ ቡድን ስንቀሳቀስበት የነበረባቸው አከባቢዎች ናቸው ተብሏልም፡፡ በመሆኑ በአከባቢው የሚገኘው አርሶ አደር ምንም አይነት ትጥቅ የሌሌውና ለየትኛውም ጥቃት ተጋላጭ ነው ሲሉም ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡ 
አስተያየት ሰጪዎቹ ጥቃቱ በተፈጸመ እለት ታግተው የተወሰዱ ሰዎች ስለመኖራቸውም ገለጸዋል፡፡ “እስካሁን ያሉት ነገር ባይኖርም ለነዚህ ለታገቱት ሰዎች ገንዘብ ይጠይቃሉ የሚል ስጋት አለ፡፡ የታገቱት ሰዎችም ሆነ የተዘረፉት የቤት እንስሳቶቹ ሰላል ኩላ ወደ ምትባል የአማራ ክልል አከባቢ ነው የተወሰዱት፡፡ ጥቃቱ ከደረሰበት አከባቢ ከሶስት ኪ.ሜ. የማይርቅ ቅርብ ስፍራ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ቀበሌው ከፍታ መነዮ ይባላል” ነው ያሉት፡፡


ግጭቱ ያስከተለው የእንቅስቃሴ መገታት   


ተመሳሳይ ግጭትና ጥቃት በሌሎች በርካታ አቅጣጫዎችም በተለይም የአማራ ክልሉ የጸጥታ ይዞታ ከደፈረሰበት ጊዜ አንስቶ ሰፍቶ እንደሚስተዋልም አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል፡፡ ይህ ሰፊ የሚባለው ጥቃት ከመከሰቱ ሁለት ቀናት በፊትም ኢሉና ጎዳጨፌ በተባሉ ቀበሌያት አቅጣጫ ሲለማ የነበረውን ሸንኮራ እና የከብት መኖ በታጣቂዎች መውደሙን ገልጸዋል፡፡ የተባባሰው የወረዳው ፀጥታ ችግር ህብረተሰቡ ኑሮውን ትቶ ወደ ከተማ አከባቢ እንዲፈልስ እያስገደደውም ነው ተብሏል፡፡ “ምንም ትራንስፖርት የለም፡፡ ሰው ወደ ወረዳ ከተማ ጉንዶ መስቀል እየፈለሰ ነው፡፡ አስቀድሞም ከዚህች ከወረዳ ከተማ ውጪ ሌሎች የወረዳው ከተሞች በጸጥታ ይዞታው ችግር ተዘግተው የሚሰጡት አገልግሎት እምብዛም አርኪ አልነበረም፡፡ በወረዳው ከሚገኙ 93 ትምህርት ቤቶች ስራ ላይ የሚገኙ ከሶስት አይበልጥም፡፡ የጤና ተቋማትም እንደዛሁ በደንብ የሚሰራ በዚህ በወረዳው ከተማ የሚገኘው ነው፡፡ የወረዳው ሰላም እየተሸሻለ ነው ብለን ስንጠብቅ ነው አሁን ደርሶ የተባባሰው፡፡ አሁን ሳምንቱን በሙሉ የትራንስፖርት ጨምሮ እንቅስቃሴው ሁሉ ከከተማው ውጪ ተገቷል” ብለዋል፡፡
ስለነዋሪዎቹ አስተያየት እና ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት ማረጋገጫና ተጨማሪ አስተያየቶችን ለመጠየቅ ለደራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽበሺ አያለው ብንደውልም ስብሰባ ላይ ነኝ በማለታቸው አስተያየታቸውን ለዛሬ ሳይሰጡን ቀርተዋል፡፡ የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ጋርም ደውለን ምላሻቸውን ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም ለዛሬ አልሰመረም፡፡


ስዩም ጌቱ 


ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር