የአሌክሲ ናቫልኒ ህልፈት፤ የምዕራባውያን ውግዘት እና የሩስያ ምላሽ
ሰኞ፣ የካቲት 11 2016የአሌክሲ ናቫልኒ ህልፈት ዜና
የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቀንደኛ ነቃፊው ፖለቲከኛ አሌክሲ ናቫልኒ በታሰሩበት እስር ቤት የመሞታቸው ዜና የተሰማው ባለፈው ዓርብ ነበር። ናቫልኒ ለዓመታት በቆዩበት የአርክቲክ እስር ቤት ሞተው የመገኘታቸውን ዜና ይፋ ያደረገው ደግሞ የሩሲያ የፌደራል ማረሚያ ቤት ነው ። ናቫልኒ “ከእግር ጉዞ በኋላ መጥፎ ስሜት ተሰምቶት ነበር” ሲሉ የእስር ቤቱ ባለስልጣናት ቢናገሩም ለሞታቸው ትክክለኛ ማረጋገጫ እንደሌላቸው አስታውቃዋል። የፖለቲከኛውን ህልፈት ተከትሎ ባለቤታቸውን ጨምሮ ምዕራባውያን የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን መንግስት ተጠያቂ አድርገዋል። ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን የዕለቱ ማህደረ ዜናችን የደፋሩ ፖለቲከኛ ህልፈት ፤ የምዕራቡ ዓለም ውግዘት ነቀፋ ትችት እና የክሬምሊን ምላሽን ከብዙ በጥቂቱ እንዳስሳለን ።
በፖለቲከኛው ህልፈት የምዕራባውያን ተቃውሞ
የ47 ዓመቱ ጎልማሳ ደፋር ፖለቲከኛ አሌክሲ ናቫልኒ ሩስያ ውስጥ በጣም ጥቂት እና ፊት ለፊት ፑቲንን በነቀፋ ከተገዳደሩ ፖለቲከኞች እና ማህበራዊ አንቂዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ ። በግልጽ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ በተአምር ተርፈው የ19 ዓመታት እስር ተፈርዶባቸው በዓለማችችን እጅጉን ቀዝቃዛ ስፍራ መሆኑ በሚነገርለት የሳይቤሪያ ግዛት ከነበሩበት የወህኒ ቤት ድንገት የሞታቸው ዜና ባለፈው ዓርብ ድንገት ሲሰማ ለውግዘቱ ምዕራባውያኑን ኃያላን መሪዎች የቀደመ አልነበረም ። የዩናትድስቴትሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሰጡት መግለጫ ፑቲንን ተጠያቂ አድርገዋል።የተካረረው የሩሲያ እና የአውሮፓ ኅብረት ውዝግብ
«የሞቱ ዜናዎች እውነት ከሆነ እና በእርግጥ መሆኑንም ላለማመን ምንም ምክንያት ባይኖረኝም፤ የሩሲያ ባለሥልጣናትም የራሳቸውን ስራ ይናገራሉ ብዬም አልጠብቅም። ነገር ግን አትሳሳቱ ፑቲን ለናቫልኒ ሞት ተጠያቂ ነው። በናቫልኒ ላይ ለሆነው ነገር ማንም አይደለም ፤ የፑቲን የጭካኔ ተግባር በድጋሚ በተግባር የተገለጠበት ነው። ሩስያ ውስጥ በሀገር ቤት ብትሉ በዓለም ላይ በየትኛውም ስፍራ ፑቲን ሊያታልሉን አይችሉም »
የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኦርሱላ ፎን ዴር ላየን በበኩላቸው ፑቲን የሚፈሩትን ሰው ገደሉ ባሉት ንግግራቸው እንዲህ ብለዋል።
« የአሌሴይ ናቫልኒ ሞት ዜና በጣም አስደንጋጭ ነው። ነገር ግን ይህ ፑቲን ህዝባቸውን ከቁብ እንደማይቆጥሩ ነው የሚያሳየው ። ፑቲን እና ጓደኞቻቸው እንደአሌክሲስ ያሉ ለነጻነት ከሚናገሩ እና ለነጻነት የሚቆሙ እና ሙስናን ለመዋጋት ከሚታገሉ ሰዎች ሌላ ምንም የሚፈሩት ነገር የለም ። አለም በአሌክሲ ናቫልኒ ሞት የነፃነት ታጋይ አጥታለች። እኛም ደግሞ ስሙን እናከብራለን ፤ በስሙ ደግሞለዲሞክራሲ እና ለእሴቶቻችን እንቆማለን።»
የጀርመኗ ሙኒክ በምታስተናግደው የዓለም የጸጥታ ጉባኤ ላይ የተገኙት የአሌክሲ ናቫልኒ ባለቤት ዩሊያ ናቫልኒ ፑቲን እና «ግብረአበሮቻቸው » ላደረጉት ሁሉ የእጃቸውን ያገኛሉ ሲሉ በሲቃ እና በእንባ ተሞልተው ተናግረዋል።ተመረዙ የተባሉት የፑቲን ዋና ተቃዋሚ ጉዳይ
«ይህ በእርግጥ እውነት ከሆነ ፤ ፑቲን ፣ ግብረአበሮቹ ፣ ጓደኞቹ እና መንግስቱ በባለቤቴ ፣ በቤተሰባችን እና ሀገራችን ላይ ለፈጸሙት ሁሉ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ማወቅ አለባቸው »
የናቫልኒ ህልፈት ከምዕራባውያን ባሻገር በሩስያ እና አውሮጳ በ,ርካታ ደጋፊዎቻቸውን ለተቃውሞ ወደ አደባባይ አስወጥቷል። ሩስያ ውስጥ ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተሰምቷል።
የሩስያ ምላሽ
የሩስያ መንግስት ባለስልጣናት ኤሌክሲስ ናቫልኒ በእስር ቤት ውስጥ በመራመድ ላይ እያሉ ራሳቸውን ስተው መውደቃቸውን እና ህይወታቸው ማለፉን ከመግለጽ ባሻገር ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ነገር ግን ዘግየት ብለው ከምዕራባውያን ለቀረበባቸውን የክስ እና ውግዘት መዓት በመንግስት ቃል አቃባይ በኩል ምላሽ ሰጥተዋል። ቃል አቃባይዋ ማሪያ ዛካሮቫ ምዕራባውያኑን በወረፉበት ምላሻቸው «እስካሁን በተጨባጭ የተረጋገጠ የፎረንሲክ የምርመራ ውጤት ይፋ ሳይሆን ምዕራባውያኑ ግን ከድምዳሜ ደርሰዋል » ሲሉ ትችት አዘል ንግግር አሰምተዋል።
የናቫልኒ ትውልድ እና ዕድገት ታሪክ
ህልፈታቸው ከተሰማበት ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ሰሞኑን በዓለም የመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ያገኙት እና ብዙ እየተባለላቸው የሚገኘው ናቫልኒ በእርግጥ እርሳቸው ማን ናቸው ? የናቫልኒ ታሪክ የሚጀምረው ከመዲናይቱ ሞስኮ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በምትገኝ ቡቲን ከተሰኘች አንዲት ትንሽዬ መንደር ውስጥ ነው ። ጊዜው ደግሞ የጎርጎርሳውያኑ 1976 ዓ/ም ። አባታቸው የቀድሞው የሶቭየት ህብረት ወታደራዊ መኮንን ናቸው ። እናታቸው ደግሞ የኤኮኖሚ ባለሞያ ፤ የበጋ ወራትን ከእናት አባቱ ይልቅ በወቅቱ የሶቭየት ሕብረት አካል በነበረችው ዩክሬን ቼርኖብል አቅራቢያ በሚገኝ ገጠራማ መንደር ከሚኖሩ አያቶቹ ጋር ማሳለፍ የሚወደው ትንሹ ናቫልኒ የከተማ እና የገጠር ቅይጥ ህይወትን እየተለማመደ እንዲያድግ ምክንያት ሆኖታል። ይህ ግን የቆየው በዩክሬኑ የቼርኖብል የኒኩልየር ማብለያ ጣብያ ፍንዳታ እስኪከሰት የጎርጎሮሳዊው እስከ 1986 ዓ/ም ድረስ ብቻ ነበር ። 10 ዓመት እስኪሞላው ። ከዚያ በኋላ ግን ናቫልኒ ገጠር ከተማ እያለ የሚያሳልፈው ጊዜ መቀጠል አልቻለም። የኒውክልየር ማብላያ ጣብያው ፍንዳታ በርካቶችን ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀሉን ተከትሎ በወላጆቹ ቤት ተወስኖ ቀረ።
የናቫልኒ የትግል ታሪክ አጀማመር
ናቫልኒ ለአሁኑ ሞጋች እና የመብት ተከራካሪነት ያደረሰውን የህግ ባለሞያነት ትምህርት የተከታተለው መዲናዪቱ ሞስኮ ውስጥ በሚገኘው ፒፕል ፍሬንድሺፕ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሩስያ ውስጥ ነው ። የመጀመሪያውን ዲግሪ በህግ ያገኘውም በ1998 ዓ/ም ነበር ። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ በመንግስታዊ የፋይናንሻል ተቋም በኤኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪውን በ2000 ማግኘት ችሏል።ሩሲያ በዩክሬን ወረራ ጀመረች
የአሌክሲስ ናቫልኒ የፖለቲካ እና ማህበራዊ አንቂነት እንቅስቃሴም የሚጀምረው ከዚሁ ከዩኒቨርሲቲ የተማሪነት ዘመኑ እንደሆነ ነው የሚነገርለት ። የመጀመሪያ የፖለቲካ ተሳትፎው የተመዘገበውም በነጻ ገበያ በሚመራ ኤኮኖሚ በሚዘወረው እና የምዕራባውያንን የሊበራል ዲሞክራሲ በሚያቀነቅነው የያብሎኮ የፖለቲካ ፓርቲን በመቀላቀል ነው።
በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የመጀመሪያዎቹ የአገዛዝ ዓመታት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዱማ ተብሎ በሚጠራው የሩሲያ የታችኛው ምክር ቤት ውስጥ የተወሰነ ስልጣን መያዝ የሚችሉበት እድል እንዳለ የመሰለበት ወቅት ነበር ። ነገር ግን 2001 ላይ በርካታ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተባበረችው ሩስያ አንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር ለመሰባሰብ መወሰናቸው የተቃውሞ የፖለቲካ ጎራውን በእጅጉ እንደጎዳ ይነገርለታል።
በዚህ ጊዜ ነው ታዲያ ወጣቱ ናቫልኒ በያብሎኮ ፓርቲ ውስጥ ወደ የአመራር አባልነት ከፍ ያለበትን ዕድል ሊያገኝ የቻለው ፤ ምንም እንኳ በፓርቲው ውስጥ በተሰጠው ኃላፊነት ከስድስት ዓመታት ብዙም ያልተሻገረ ጊዜ ቢያሳልፍም ። ናቫልኒ ፓርቲውን በጽንፈኛ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ውስጥ አስገብቶ ጉዳት አድርሶበታል በሚል ከፓርቲው እንዲሰናበትም ምክንያት ሆነ። ናቫልኒ ግን በወቅቱ የቀረበበትን ውንጀላ አልተቀበለም ። ከፓርቲ ኃላፊነቱ ለመባረሩ ከፓርቲው መሪ ግሪጎሪ ያቭሊንስኪ ጋር በግል ጉዳይ ግጭት ውስጥ መግባቱን ተከትሎ እንደሆነ ተናግሮ ነበር።የሩሲያ ክተትና የምዕራባዉያን ዉግዘት
አሌክሲስ ናቫልኒ ከሩስያም አልፎ በተቀረው አለም አይነተኛ እና ተገዳዳሪ የፖለቲካ እና የማህበራዊ አንቂ ሆኖ የታየው በጎርጎርሳውያኑ 2008 ነበር ።
ከሩስያ ባለስልጣናት ጋር መጋፈጥ
በመንግስት የንግድ ኩባንያዎች ውስጥ የሚከናወኑ ምዝበራዎችን ለማጋለጥ ያመቸው ዘንድ ከየንግድ ኩባንያዎች አነስተኛ የአክሲዮን ድርሻዎችን በመግዛት በባለአክሲዮኖች ስብሰባ ላይ መሳተፍ የሚያስችለውንም መንገድ ጠረገ ።
ያሰበው ፣ ከውጭ ሆኖ ሲሰማው የነበረው የፋይናንስ ሪፖርት አለመመጣጠን በእርግጥ እንዳለ በአካል ተገኝቶም አረጋገጠ። በየኩባንያው የአስተዳደር እና የሂሳብ አያያዙ ብልሹ መሆኑንም አረጋገጠ። ይህ የወጣትነት ዕድሜውን ጨርሶ ወደ ጉልምስናው በመግባት ላይ ለነበረው ናቫልኒ እስከሞት ሊያደርሰው የሚችለውን መንግስትን ፊት ለፊት የመተቸት ፣ ብልሹ አሰራሮችን የማጋለጥ እና ብሎም ፕሬዚደንቱን ሳይቀር የመንቀፍ የማህበራዊ አንቂ ፖለቲከኝነት መንገድን መከተል መረጠ። ናቫልኒ የሚያጋልጣቸው የመንግስት ተቋማት ብልሹ አሰራሮች የበርካታ ሩስያውያንን ጆሮ እና ቀልብ መግዛት ችሏል። የትንታጉ ፖለቲከኛ የማህበራዊ አንቂነት ሚና በርትቶ ዲሜትሪ ሜድቬዴቭ ከጎርጎርሳውያኑ 2008 እስከ 2012 ወይም ፑቲን በድጋሚ እስኪመለሱ ድረስ በስልጣን በቆዩበት ወቅት መንግስታቸው የተብጠለጠለበትን ብልሹ አሰራር እስከመቀበልም አድርሷቸው ነበር። ሜድቬዴቭ በወቅቱ ከመንግስት የግዥ ስረዓት ውጭ በሚፈጸም መመዝበር ሀገሪቱ በየዓመቱ እስከ አንድ ትሪሊዮን ሩብል ወይም እስከ 31 ቢሊዮን ዶላር እንደምታጣ አምነዋል። ይህ ደግሞ አይን እና ጆሮ እየገዛ ለመጣው ትንታጉ ፖለቲከኛ የተደማጭነት ደረጃውን አንድ እርምጃ ወደፊት እንዳራመደው ይነገርለታል።
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ናቫልኒ ራሱን ለሞስኮ ከንቲባነት ማዘጋጀቱን እና ለውድድር እንደሚቀርብ ይፋ ያደረገው ። በጎርጎርሳውያኑ ሀምሌ 2013 ይህንኑ ሃሳቡን ለደጋፊዎቹ ይፋ ሲያደርግ ከመንግስት ያገኘው ምላሽ ግን በተቃራኒው ነበር ። የናቫልኒ ለከንቲባነት የመወዳደር ዝግጁነት ስጋት የገባው የክሬምሊን መንግስት ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የገንዘብ ማጭበርበር ፈጽመሃል በሚል ፍርድቤት እዲቀርብ እና አምስት ዓመት በእስራት እንዲቀጣ አስፈርዶበታል። ይህ በቅርብ ጊዜ የሩስያ የተቃውሞ ፖለቲካ ታሪክ ገዝፎ የታየ እና መንግስትን ለመቃወም በርካታ ደጋፊዎችን አደባባይ እንዲወጡ ያደረገበትን አጋጣሚም ፈጥሯል። በወቅቱ ብርቱ ተቃውሞ ያስከተለው የእስር ፍርድ አይሎ ናቫልኒ ይግባኝ ሳያሰማ በቀጣዩ ቀን ከእስር እንዲወጣ ከማድረጉም በላይ ለከንቲባነት ለመወዳደር የያዘውን ውጥን አጠናክሮ እንዲገፋ መንገድ ጠርጎለታል። ናቫልኒ ምንም እንኳ በከንቲባነት ተወዳድሮ ማሸነፍ ባይችልም ዘብጥያ እስኪወረወር ድረስ አይነኬው እና አይምሬው ፑቲንን ፊት ለፊት መተቸት እና መንቀፍ ግን አላቆመም ነበር። ፖለቲከኛው ከምዕራባውያን የሚያገኛቸው ድጋፎች ደግሞ ከመንግስት ጋር አይንና ናጫ ወደ ሚያደርጋቸው አዲስ ምዕራፍ ተሸጋገሩ ።ሞስኮን ከምዕራባውያን ያፋጠጠው የሩሲያ አራት ግዛቶች ግንጠላ
ምስክርነት
ዶ/ር ለማ ይፍራ ሸዋ በጀርመን ሀገር ረዥሙን ህይወታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት የተወሰነ ጊዜ ቆይተው ነበር። የሀገሪቱን ማህበረ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በቅርበት ለመከታተልም ምክንያት ሆኗቸዋል። የአሌክሲ ናቫልኒን ህልፈት አስደንጋጭ ነበር ።
«በእውነት በጣም ነው የደነገጥኩት ። አንድ የ47 ዓመት ጎልማሳ ራዕዩን ሃሳቡን ለሃገሩ ፤ ራሽያ በጣም ታላቅ ሀገር ናት ። ወደ 145 ሚሊዮን ነዋሪ ያላት ፤ በጣም ታላቅ ሀገር በጣም ሀብታም ሀገር ነች። ከዚያ ህዝብ መሃል ይሄ ጎልማሳ የሀገሬ ፖለቲከኞች በሙስና ተጨማልቀው ፤ መሰረተ ልማቶች በፈራረሱበት ፣ እነርሱ ታላላቅ መንደላቀቂያ ህንጻ ይሰራሉ፤ ዘመናዊ መኪና ይነዳሉ፤ ህዝቤ ተቸግሯል በሚል የራሽያን ወጣቶች በማነሳሳት ፕሬዚዳንት ፑቲንን ስጋት የጣለ ነበር።»
አሌክሲስ ናቫልኒ የሩስያን መንግስት በተወሰነ መልኩ መገዳደር መጀመሩ ለነርቭ መርዝ ጥቃት አጋልጦታል። ይህ ደግሞ በጎርጎርሳውያኑ 2020 ለሚደረገው አካባቢዊ ምርጫ እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት ነበር። ከፈጣሪ በታች ምስጋና ለጀርመኖቹ ይሁንና ህይወቱ በተዓምር ተረፈችለት። እንደዚያም ሆኖ ግን ናቫልኒን ወደ ሩስያ ከመመለስ እና ፑቲንን ፊት ለፊት ከመጋፈጥ አልገታውም። ዉሳኔው ብዙዎችን ሳያስገርም አልቀረም ፤ ህይወቱን ለአደጋ አሳልፎ መስጠት የለበትም የሚሉ ድምጾች ከፍ ብለውም ይሰሙ ነበር።ምዕራባውያን ናቫልኒ እንዲፈታ ጥሪ አቀረቡ
ዶክተር ለማ እንደሚሉት ናቫልኒን ወደ ሀገር ቤት መመለስ ነበረበት ወይም መቅረት ነበረበት ለሚለው በእርሱ ሁኔታ ውስጥ መሆንን ይጠይቃል ይላሉ ።
« ከዳነ በኋላ ወደ ሃገር ቤት ይመለስ አይመለስ ነብሱን ይማረው እና ፤ ልክ ነው ልክ አይደለም ለማለት በእርሱ ጫማ ውስጥ ሆኜ ነው የምወስነው ። አንድ ሰው ለቆመለት ዓላማ አይሆንም ብሎ መሳሪያ አንስቶም ይታገላል። »
የሆነ ሆኖ አሌክሲስ ናቫልኒ ፣ መታመሙ ሳይሰማ ፣ ወደ ህክምና መወሰዱም ሳይዘገብ ከዚያ ለሰው ልጆች በህይወት መቆየት ፈተና ከሆነበት በረዷማ ምድር የህልፈቱ ዜና ተሰማ ። ደጋፊ ናቫልኒ ሩስያውያንን ጨምሮ ምዕራባውያንን በአንድ ድምጽ በተቃውሞ እና ነቀፌታ ሩስያ ላይ እንዲዘምቱባት ምክንያት ሆነ። ሩስያ ግን ወይ ፍንክች ።
የማህበራዊ አንቂው እና ፖለቲከኛው አሌክሲስ ናቫልኒ ህልፈት በሩስያ የውስጥ ፖለቲካ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይኖረው ይሆን ?
ዶ/ር ለማ አይመስለኝም ይላሉ ።
«ራሽያ በጣም ሀገሩን የሚወድ ህዝብ ነው ። ሁለንተናዊ አንድ ህዝብ ነው፤ እና ይሄ ከዩክሬን ጋር በሚደረግ ጦርነት ሀገር ቤት ውስጥ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ዱማ ላይ የወንበር ሽኩቻ ላይ ለሚደረገው ትግል ይህን ያህል ትልቅ ሚና ይጫወታል ብዬ አልገምትም። »
የናቫልኒ ወላጅ እናት እና ጠበቃቸው የልጃቸውን አስክሬን ለመሻት ሳይቤሪያ ውስጥ ወደሚገኘው ወህኒ ቤቱ ቢያመሩም እስካሁን የአባ ከና ያላቸው የለም ። ስለቀብሩም በተመለከተ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰአት ድረስ የተባለ ነገር የለም ።
አሌክሲ ናቫልኒ አሁን በህይወት የሉም ። ሲሟገቱላት የነበረችው ሩስያ እና ሩስያውያን ግን በኃያሉ ቭላድሚር ፑቲን መሪነት አሉ ። ሩስያ ትፋጃለች ፤ ሳይቤሪያ ትቀዘቅዛለች፤ ህይወት ግን ይቀጥላል።
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ