1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

የእሥራኤል ፍልስጥኤም ደም አፋሳሹ ግጭት ቀጥሏል

ረቡዕ፣ ሰኔ 14 2015

የእሥራኤል ፍልስጥኤም ግጭት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ምዕራብ ዮርዳኖስ ውስጥ እጅግ ተባብሶ ቀጥሏል ። በሁለቱም በኩል የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት እንዲቀጠፍም ሰበብ ሆኗል ። ዳግም ስላገረሸው የእሥራኤል ፍልስጥኤም ግጭት ሰበብ እና አንደምታውን በተመለከተ የተደረገ ቃለ መጠይቅ ።

https://p.dw.com/p/4St63
Westjordanland | Israelischer Militäreinsatz in Jenin
ምስል Nedal Eshtayah/AA/picture alliance

ያገረሸው ግጭት እጅግ እንዳይባባስ አሥግቷል

ሄድ መለስ የሚለው የእሥራኤል እና የፍልስጥኤም ግጭት ዳግም በምዕራብ ዮርዳኖስ ከሰሞኑ ጠንከር ብሎ አገርሽቷል ። የእሥራኤል መከላከያ ሠራዊት አራት እሥራኤላውያን የገደሉ የፍልስጥኤም ታጣቂዎችን ቤት ለማፍረስ በሚል በኃይል በተያዘችው ምዕራብ ዮርዳኖስ ተጨማሪ ኃይል ዛሬ መላኩ ተዘግቧል ። የእሥራኤል መንግሥት ጥቃቱን ያደረሱት «ከሐማስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች» ናቸው ብሏል ። ግድያው ትናንት የተፈጸመው ጄኒን ከተማ ውስጥ ሰባት ፍልስጥኤማውያን በጄኒን የስደተኞች መጠለያ ውስጥ በእሥራኤል ወታደሮች ጥቃት ከተገደሉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው ።  

ምዕራብ ዮርዳኖስ፤ የእሥራኤል ጦር ጄኒን ውስጥ ጥቃት ካደረሰበት ሥፍራ በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ሲወጣ የፍልስጥኤማውያን ጓዳ ሠራሽ ፈንጂ በአጠገቡ ፈንድቶ
ምዕራብ ዮርዳኖስ፤ የእሥራኤል ጦር ጄኒን ውስጥ ጥቃት ካደረሰበት ሥፍራ በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ሲወጣ የፍልስጥኤማውያን ጓዳ ሠራሽ ፈንጂ በአጠገቡ ፈንድቶምስል Nedal Eshtayah/AA/picture alliance

ምዕራብ ዮርዳኖስ ውስጥ በሚገኘው የኤሊ ሠፈራ መንደር የተገደሉት እሥራኤላውያን ከ64 ዓመቱ አዛውንት በስተቀር ሦስቱ ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች ነው ተብሏል ። በሔሊኮፕተር ጭምር የታገዘው የእሥራኤል ጦር ምዕራብ ዮርዳኖስ ጄኒን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ ባደረሰው ጥቃት ከተገደሉት ፍልስጥኤማውያን ወጣቶች መካከል ደግሞ የ15 ዓመት ታዳጊም ይገኝበታል ተብሏል ። በጥቃቱ 91 ፍልስጥኤማውያን መቁሰላቸውም ተዘግቧል ። የጄኒን የስደተኞች መጠለያ የተመሰረተው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1953 ነው ።

ብርቱው ደም አፋሳሽ ግጭት የተቀሰቀሰው የእሥራኤል ጦር ሰኞ ሰኔ 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ማለዳ የፍልስጥኤም ጄኒን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያን ድንገት በመውረር ጥቃት ካደረሰ በኋላ ነው ተብሏል ።  የእሥራኤል ጦር የስደተኛ ጣቢያውን ወርሮ ጥቃት ያደረሰው ሁለት «ተጠርጣሪ ታጣቂ» ፍልስጥኤማውያንን በቁጥጥር ስር ለማዋል ነው ብሏል ። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንደኛው ከስድስት ወር በፊት ከእስር የተለቀቁት የቀድሞው የፍልስጥኤም እስረኛ ዓሰም አቡ አል ሐይጃ ይገኙበታል ተብሏል ። 

የእሥራኤል ፍልስጥኤም ግጭት ዳግም ያገረሸባት ምዕራብ ዮርዳኖስ
የእሥራኤል ፍልስጥኤም ግጭት ዳግም ያገረሸባት ምዕራብ ዮርዳኖስምስል Majdi Mohammed/AP Photo/picture alliance

የተባባሰው ደም አፋሳሽ ግጭትን ተከትሎ የእሥራኤል ቀኝ አክራሪ መንግሥት በምዕራብ ዮርዳኖስ መጠነ ሰፊ ዘመቻ እንዳይከፍትም አስግቷል ። አንዳንዶች ከወዲሁ ጥሪውን እያስተላለፉ መሆኑም ተሰምቷል ። የግጭቱ መቀስቀስ ሰበብ እና አንደምታውን በተመለከተ በእሥራኤል እየሩሳሌም የመካከለኛው ምሥራቅ የዶይቸ ቬለ ዘጋቢ ዜናነህ መኮንን ማብራሪያ ሰጥቷል ። 

ቃለ መጠይቁን ከድምፁ ማእቀፍ ማድመጥ ይቻላል

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዜናነህ መኮንን

እሸቴ በቀለ