1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የከያንያን እና የኪነ-ጥበብ መድረኮች ጥበቃ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 17 2016

በኪነ-ጥበብ ሥራዎች እና ባለሙያዎች ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንዲቆሙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ለመንግሥት ጥሪ አቀረበ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እና መድረኮች ላይ "ወከባዎች፣ ክልከላዎች፣ እሥር እና ጫናዎች ከእለት እለት እየበረቱ መምጣታቸው" እንዳሳሰበውም አክሏል።

https://p.dw.com/p/4gHSJ
የአዲስ አበባ ማዘጋጃቤት
የአዲስ አበባ ማዘጋጃቤትምስል Seyoum Getu/DW

የከያንያን እና የኪነ-ጥበብ መድረኮች ጥበቃ

እንዳይታዩ የታገዱ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች እና የባለሙያዎች እሥር
ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ጥቅም ያላቸው የኪነ-ጥበብ ሥራዎች በመድረክም ይሁን በሌሎች አማራጮች በሙዚቃ፣ በትያትር፣ በግጥም ፣ በሥዕል ፣ በቅርጻ ቅርጽ የሚያንፀባርቋቸው ሃሳቦች የዜጎች ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ማሳያዎች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ገልጿል።
ማዕከሉ ወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሰው "ቧለቲካ" የተባለው የመድረክ ትያትር ጥር ላይ በመንግሥት እንዳይታይ መታገዱን፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሰው "እብደት በሕብረት" የተባለው ሌላኛው የመድረክ ተውኔት ተዋናይ እና አዘጋጁ መታሠራቸውን አስታውቋል።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም የኪነ ጥበብ ሥራዎችና ባለሙያዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው እንጂ ሊገቱ አይገባም ብለዋል። "አርቲስቶች አንዳንዱ ሥራቸው ሲስተጓጎል፣ ፕሮግራማቸው ሲሰረዝ ፣ የተወሰኑት ደግሞ እሥር እና መጉላላት ሲደርስባቸው እየተመለከትን ነው"

መሰል ሥራዎች የሚቀርቡባቸው መድረኮች "የስብሰባ ፈቃድ ያስፈልጋል" በሚል ባለሙያዎች መስተጓጎል እየገጠማቸው መሆኑን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል፣ ይህን መሰሉ ድርጊት እንዲገታ ጠይቋል።

"ምህዳሩ በዚህ ደረጃ የሚጠብ ከሆነ እንደ ሀገር ጉዳት ያስከትላል"
ዘርፋን በእኩልነት መጠቀም እንደሚያስፈልግ መጠየቁ
መንግስት የሚፈልጋቸው ፊልሞች፣ የኪነ ጥበብ ሥራዎች በመንግሥት የቁሳቁስ ድጋፍ ተሰርተው በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ጭምር ሲቀርቡ ይታያል። በሌላ በኩል ክልከላዎች ይታያሉ። ይህንን ጉዳይ አንስተን የጠየቅናቸው አቶ ያሬድ ኃይለማርያም "መንግሥትን የሚደግፉ ሰላማዊ ሰልፎች ያለምንም ችግር በመላ ሀገሪቱ ይካሄዳሉ። ግን ደግሞ ከመንግሥት ውጪ የሚካሄዱ፣ በመንግሥት ፖሊሲ እና አካሄድ ላይ ቅሬታ ያላቸው ሲሆኑ ሰላማዊ ሰልፎቹ እንዳይካሄዱ ይደረጋል። ሰልፎቹንም ያዘጋጁት ለእሥር ይዳረጋሉ፣ ከሀገር የሸሹም አሉ" በማለት በኪነ-ጥበብ መስክም ተመሳሳይ ነገር እየተስተዋለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"እንዲህ ያለው ወከባ ሲመጣ ባለሙያዎቹ ራሳቸውን ወደማቀብ ይመጡና በነፃነት ማሕበረሰቡ የሚፈልጋቸውን መልእክቶች ከማስተላለፍ ይልቅ በሌሎች መዝናኛዎች ፣ አንዳንዶቹም ከመስኩ ሊወጡ ይችላሉ"


የመብት መከበርን በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የማስተማር ጥረት
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል እንዲህ ያሉ  ድርጊቶች እንዲቆሙ ፣ መንግሥት ሃሳብ በነፃነት የሚገለጽባቸውን መሰል ዘርፎች እንዲጠብቅ እና የታሰሩትንም እንዲፈታ ጠይቋል።
በአሁኑ ወቅት "እብደት በሕብረት" የተባለው የመድረክ ትያትር ተዋናይ አማኑኤል ሀብታሙ እና አዘጋጁ ዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳ የታሰሩ ሲሆን ገጣሚ በላይ በቀለ ወያም - ለረጅም ጊዜ በእሥር ላይ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ የፊልም ፌስቲቫል በማዘጋጀት ላይ ሲሆን፣የሰብዓዊ መብቶች በስፋት በኪነ ጥበብ ሥራዎች ውስጥ ትኩረት አግኝተው እንዲዳሰሱ ማድረጉ "ሰብዓዊ መብቶች ባሕል የሆኑባት ኢትዮጵያን" ማየት የሚለውን ራዕዩን ለመሳካት አቅም የሚሰጠው መሆኑ በማመን የሚያዘጋጀው እንደሆነ አስታውቋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር