በኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን የፈተነው የመረጃ እጦት
ረቡዕ፣ መስከረም 23 2016በኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች በተለያዩ አጋጣሚዎች ዘገባ ሲያሰናዱ በመረጃ እጦት እንደሚፈተኑ ሲገልጹ ይስተዋላል፡፡የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ የመረጃ እጦቱ ህዝብን ላልተጠራ እና ለሀሰተኛ መረጃዎች ስለሚዳርግ ፈተናው ይከፋል ይላሉ፡፡ ግጭት መፈናቀል በሚዘወተርባት ኢትዮጵያ የዜጎችን ሰቆቃ መስማት የሁል ጊዜ ዜና ቢሆንም ስለ ግጭቶቹና ግጭቱን ተከትሎ ስለሚመጣው ጉዳት መሰረታዊ መንስኤ መረዳት ግን ቀላል አይሆንም፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ከስር መሰረቱ በመንግስታዊ ተቋማት ኃላፊነቱን በመውሰድ ለዜጎች የጠራ ወቅታዊ መረጃ በመስጠት ረገድም የበዛ መታተር አይታይም፡፡ በበርካቶች እምነት ይህ ደግሞ በአገሪቱ ሀሰተኛ መረጃዎች እየተስፋፉ ችግሮችን እንዲፈጥሩ አንደኛው ምክንያትም ነው፡፡
ለአብነትም በቅርቡ እንኳ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ) በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች ለሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መንግስት ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም ሲል መተቸቱ ይታወሳል፡፡ ሰብዓዊ ተቋሙ የመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች እና ታጥቀው መንግስትን የሚወጉ አካላት ተጠያቂ ናቸው ቢልም በመንግስት በኩል መሰል ክሶች ላይ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ እንኳ ሲሰጥ አይደመጥም፡፡ ከመንግስት ጋር ቅርበት ያላቸው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንም ስለ ሚፈጸሙ ግድያ እና ቀውሶቹ ሲዘግቡ ጎልቶ አይሰማም፡፡
የመረጃ እጦት በኢትዮጵያ
መንግስት መሰል ክስተቶች ሲፈጠሩ ዝምታን ለምን ይመርጣል? መረጃዎቹን በግልጽ እና ወቅቱን ጠብቆ አለመስጠትስ ጉዳቱ ወይስ ትርፉ ይጎላ ይሆን?
ጋዜጠኛ ሲሳይ ሳህሉ በኢትዮጵያ የግሉ ፕሬስ ለዓመታት በጋዜጠኝነት ሰርቷል፡፡ በሙያው ስለሚያጋጥመው የመረጃ እጥረት እና ፈተናውም ይህን አስተያየት አጋርቷል፡፡ “በተለይም ከሰሜን ኢትዮጵያው የህወሓት እና ፌዴራል መንግስት ጦርነት ወቅት የሆነውን ቀንጨብ አድርገን ብንመለከተው በህወሓት በኩል ለኮሚዩኒኬሽን ስራው ሰፋ ያለ ስፍራ ሲሰጥ በፌዴራል መንግስት በኩል ደግሞ ያ ጎልቱ አይስተዋልም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና መገናኛ ብዙሃን ስለጦርነቱ የተዛባ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስቻለ ይመስለኛል፡፡ ይህ የሚሆነው የመንግስት አካላት መረጃን የመስጠት ጥቅም ካለመረዳት፣ መረጃን ለህዝብ መስጠት ግደታም እንደሆነ ካለመረዳት ይመስላል፡፡ ከዛም ባለፈ አንዳንዴ ለመረጃ ደውለህም ስድብም የምታስተናግድበት አጋጣሚ ይኖራል” ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያች ማኅበር ሰብሳቢና በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ስራ ውስጥ የካበተ ልምድ ያለው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩሉ በሰጠን አስተያየት በኢትዮጵያ ውስጥ መረጃን የማግኘት ፈተናው ጋዜጠኞችን ለዓመታት ሲያስቸግር የቆየና አሁንም ድረስ ሊቀረፍ ያልቻለ ችግር ነው ይላል፡፡ “ይህ ችግር ህዝብን፣ መንግስትን እና መገናኛ ብዙሃንን የሚጎዳ ተግባር ነው፡፡
ዝብ መረጃ የማግኘት መብቱን እየተነፈገ፣ መንግስትም ከህዝብ ጋር በስርዓት የሚገናኙት ተቋማትና አካላት ሲያጣ ህዝብና መንግስትን የሚያገናኝ ድልድይ ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ ከዚያ ውጪ ደግሞ መገናኛ ብዙሃንም የተቋቋሙበትን መረጃን የማቀባበል ስራቸውን በአግባቡ የመወጣት ኃላፊነት ያጣሉ፡፡ ያ ለሚዛናዊነት እጦት ችግርም ይዳርጋቸውና ሁሉም ተጎጂ ይሆናሉ ማለት ነው” ይላል ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ።ባለሙያዎቹ በአስተያየታቸው ቢሆን ያሉትን ምክረ-ሃሳባቸውንም አጋርተውናል፡፡
ጋዜጠኛ ሲሳይ ሳህሉ “በመንግስት እና ህዝብ መካከል ያለው የመረጃ ልውውጡ ካልተጠናከረ ልዩነታቸው እየሰፋ ይመጣል፡፡ የመንግስት ተቋማት የህዝብ ግንኙነት በማጠናከር መረጃን ለህዝብ መስጠት ግዴታ እንደሆነ ሊያሰለጥኑዓቸው ይገባል፡፡ አሁንም በዚህ ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ልዩነቱን በማጥበብ ረገድ ደግሞ ትልቁ ስራ ሚጠበቀው ከመንግስት ይመስላል” ብሏል፡፡የተፈናቃዮች ብዛትና የመረጃ እጥረት
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በፊናው “እምባ ጠባቂ ተቋም ሁልጊዜ ከመገናኛ ብዙሃን ጎን እንደቆመ አውቃለሁ፡፡ አቤቱታዎችን ያስተጋባል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤትም ችግሩን ለመቅረፍ ብዙ እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት፡፡ እኔ የምመራው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበርም በተደጋጋሚ የችግሩን መኖር እያሳወቀ ይገኛል፡፡ አሁንም ቢሆን ማህበራችን ህዝብ መረጃን ማግኘት መብቱ እንዲከበር አበክሮ ይሰራል፡፡ የሰብዓዊ መብት ተቋማትም ይሄንን መጠየቅ አለባቸው። መንግስትም በኮምዩኒኬሽን መስሪያ ቤቱ በኩል መንቀሳቀስ አለበት። እንደ ህዝብም ከአሉባልታ እና ሀሰተኛ ወሬ መዳን የሚቻለው መረጃን በወቅቱ በመስጠት ነው” ሲል ይመክራል፡፡
ዶቼ ቬለ በኢትዮጵያ በየጊዜው ስለሚፈጠሩ ግጭቶችና ግጭቱን ተከትሎ ስለሚከሰቱ አደጋዎች ከመንግስት አካላት ማረጋገጫዎችን ለማግኘት ሁሌም ይጥራል። ዛሬ ያነሳነው የመረጃ እጦት ችግርን በተመለከተም መንግስት አስተያየቱን እንዲሰጥበት ለመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገለግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ብደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ አስተያየታውን ማካተት አልተቻለም፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ